“ሁሌም በልባችን ናችሁ!” – “ተረጂዎችን በዘለቄታ ለማቋቋም የሚያስችል፤ ግልጽነት ያለው ተጎጂዎችን ያሳተፈ ከመንግሥት ተጽዕኖ ነፃ የሆነ ኮሚቴ መቋቋም አለበት”


(ይድነቃቸው ከበደ)

የተጎዱ ወገኖቻችንን እግዚአብሔር ያፅናችሁ ለማለት ከሁለት ቀን ቆይታ በኋል በድጋሚ ሄጃለው። መቼም የእኛ ነገር ! ከሆነ በኋል መሯሯጥ የምንግዜም ተጋባራችን ነው ። ይህም ቢሆን አይከፋም ፣ ቀድመን ባንደርስም ከሆነ በኋል ፣ ለሆነው ነገር የሚቻለንን ማድረግ ክፋት የለውም። የሞቱትን ወገኖቻችን መመለስ ባይቻልም፣አሁን በቦታው ላይ የሚታየው አጋርነት እና የሰብዓዊ እርዳት እጅግ በጣም ደስ ይላል። ወገኖቻችን በተጠለሉበት ቦታ እንዲሁም ሐዘን በተቀመጡበት ዱንካን ውስጥ ፣የሚታየው የሰው ብዛት እና ወገናዊነት ለተጎጂ ቤተሰቦች ብርታትና ጽናትን የሚሰጥ ነው። ይሁን እንጂ የዛሬ ሳምንት በመንግሥት ግዴለሽነት እና ቸልተኝነት ብቻ ከ120 የማያንሱ ወገኖቻችን ህይወት የጠፋበት ቦታ እንደነበረ አሁን ድረስ ጥሎት የሄደው አሻር አልጠፋም፣ወደፊትም የሚጠፋ አይደለም ።

በአካባቢው የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች እና ተሽከርካሪዎች አሁንም በቦታው አሉ ። የፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሌላው ጊዜ ቁጥራቸው አነስተኛ ነው። ክልከላ ይደረግባቸው የነበረ ቦታዎች በቅር እርቀት እየተንቀሳቀሱ ማየት ለሚፈልግ በፊት ይከለከል እንደነበረ አሁን አይከለከለም ። ሆኖም ግን አደጋው ወደ ደረሰበት ቦታ ዘልቆ መግባት ክልክል ነው ። አደጋው በደረሰበት ቦታ፣ የመቆፈሪያ ማሽኖች ፣ገልባጭ መኪናዎች ፣ ፖሊሶች እንዲሁም የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች እና የተወሰኑ ሰዎች፣ በሥራ ተጠምደው ሲንቀሳቀሱ ይታያል።

[ads_center_news]

በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ሰዎችን ጠይቄ እንደመለሱልኝ ከሆነ ፣ ከተነዳው የቆሻሻ ክምር ውስጥ ፣ በህይወት ያለ ሰውን የማግኘት እድል ከባድ ቢሆንም፣ የሞተ ሰው ሊኖር ስለ ሚችል ፍላጋው በደንብ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በማለት በአካባቢው ለሚገኙ የመንግስት ተጠሪዎች ጥያቄ እንዳቀረቡ ገልጸውልኛል ። በቀረበው ጥያቄ መሰረት ፍላጋው እየተካሄደ ነው። በተለይ አደጋው በደረሰበት አካባቢ ሰዎች በብዛት የሚኖሩበት ቦታ፣ በመለየት ፍለጋው እየተካሄደ ነው። በፍለጋው ሥራ ላይ ቻይናዊያን የመቆፈሪያ ማሽኖችን በማቅረብ እገዛ እድርገው እንደነበረ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸውልኛል ።


ቆሻሻው ከተደረመሰበት ፊትለፊት በሚገኙ በመደዳ በተሰሩ ቤቶች ፤ እንዲሁም ከቤቶቹ በስተቀኝ በዋናው መንገድ ዳር ላይ፤ በህይወት የተረፉ ፣ ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው የሟች ቤተሰቦች ለቅሶ ተቀምጠው ይገኛሉ። እዚያው አካባቢ የጎረቤቶቻቸውን ቤት መጠለያ ያደረጉ በርካቶች ናቸዉ ። እነሱ ባሉበት ተከታታይ በቁጥር አራት በሚሆኑ ጊቢ ውስጥ ፣ በግለሰቦች ተነሳሽነት በተለያዩ መኪናዎች የተጫኑ ፣ የታሸጉ ብዛት ያላቸው ውሃ ፣የንጽህና መጠበቂያ ፣የተለያዩ አልባሳት ፣ እና የታሸጉ ምግቦች ለተጎጂ ቤተሰቦች ለማድረስ ይደረግ የነበረው ጥረት ለመመልከት ችያለው።

የቆሼ ሰፍር ወጣቶች ፣ የደረሰባቸው ሐዘን ከፊታቸዉ ላይ አልጠፋም፣ ዓይናቸው እንባ እያቀረረ ፣ “ሁሌም በልባችን ናችሁ !” የሚል ጥቁር ፖሎ ቲሸርት ለብሰው፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን ለማፅናናት እና ለመርዳት እንዲሁም ሁኔታውን ለማየት ለሚመጣ ፣ በተለምዶ አጠራር ከ02 ወይም ከዋናው መንገድ አንስቶ አደጋው እስከ ደረሰበት ቦታ ድረስ ፤ መንገድ በመምራት፣ የድንገተኛ ሠራተኞን በመርዳት፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች የሚሰጥ ምግብና ውሃ እንዲሁም ቁሳቁስ በመሸከም እና በማመላለስ፣ ሐዘንተኞችን በማጽናናት፤ በህይወት ለተረፋቱ ወገኖቻችን የሚያደሩጉት እገዛና ድጋፍ እጅግ በጣም የሚደነቅ እና የሚበረታታ ነው።

በአካባቢው በነበረኝ ቆይታ ከተገነዘብኩት ነገር በመነሳት ፣ የምስጠው የግል አሰተያየት።የተጎጂ ቤተሰቦችን ለመርዳት ፣ በግለሰቦች እና በተቋማት የሚደረገው እርዳታ የሚበረታታ ቢሆንም ፣የእርዳታው አሰባሰብ እንዲሁም የተሰበሰበው እርዳታ መልሶ ለተጎጂዎች የሚደርስበት ሂደት በአግባቡ ሊከናውን ይገባል። በተለይ በተጎጂዎች ስም የሚሰበሰበው እርዳት ለተጎጂ ቤተሰቦች በትክክለኛው መንግደ መድረሱ ሊረጋገጥ ይገባል። የእርዳታ አሰባሰቢ እንዲሁም እርዳታውን ለተረጂዎች የሚያደርሱ ፣ ተረጂዎችን በዘለቄታ ለማቋቋም የሚያስችል፤ ግልጽነት ያለው ተጎጂዎችን ያሳተፈ ከመንግሥት ተጽዕኖ ነፃ የሆነ ኮሚቴ መቋቋም አለበት። ከመንግስት ጀምሮ እስከ ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች ጭምር ፣ በተረጂዎች ስም የተሰበሰበው ገንዘብ እና ቁሳቁሱ ለብክነት እና ለግል ጥቅም እንዳይውል ስጋት አለኝ።ህይወታቸውን ላጡ ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማር ፤ ለቤተሰቡና ለወዳጅ ዘመድ መጸናናት ፈጣሪ ይስጥልን ፤ አሜን!!!

Leave a Reply

Be the First to Comment!

avatar
wpDiscuz